መቀሌ 70 እንደርታ በማውሊ ስህተት ከውድድሩ ተሰናብቷል

መቀሌ 70 እንደርታ በማውሊ ስህተት ከውድድሩ ተሰናብቷል
ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ እየተሳተፈ የነበረው መቀሌ 70 እንደርታ በኢኳቶሪያል ጊኒው ካኖ ስፖርት በድምር ውጤት 3ለ2 በሆነ ውጤት ተሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ሳያልፍ ቀርቷል ።

ምዓም አናብስቶቹ መቀሌዎች በመጀመሪያው ጨዋታ ከሜዳቸው ውጭ ኢኳቶሪያል ጊኒ ላይ በተካሄደው ጨዋታ በካኖ ስፖርት 2ለ1 ተሸንፈው ሲመለሱ ውጤቱን በሜዳቸው ቀልብሰው ወደ ቀጣዩ ዙር እንደሚያልፉ የተጠበቀ ቢሆንም ሳይሆን ቀርቷል ።

በርካታ ደጋፊዎች ታድመውበት በትግራይ ስታዲየም መቀሌ 70 እንደርታ ከ ካኖ ስፖርት ጋር ዛሬ ያደረጉት ጨዋታ 1ለ1 በመጠናቀቁ ባለሜዳዎቹ በአሳዛኝ ሁኔታ ከውድድሩ ሲሰናበቱ ካኖ ስፖርት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል ።

በጨዋታው ሁለት ጎሎች ሲቆጠሩ በሁለተኛው አጋማሽ አንድም ጎል አልተቆጠረም ።ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ነበር 1ለ1 በሆነ ውጤት ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩት።

አማኑኤል ገ/ሚካኤል በ11ኛው ደቂቃ ምዓም አናብስቶችን መሪ ያደረገበትን ድንቅ ጎል ሲያስቆጥር በ37ኛው ደቂቃ ቤንጃሚን የእንግዳዎቹን ካኖ ስፖርቶች የአቻነትቷን ጎል አስቆጥሯል ።

መቀሌዎች በድጋሚ ወደ መሪነት የሚመለሱበትንና ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያልፉበትን ወርቃማ የፍፁም ቅጣት ምት ማውሊ ሳይጠቀምበት መባከኑ እጅግ የሚያስቆጭ ሁኗል ።

የምዓም አናብስቶቹ ጎል አዳኝ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ሁለት ጎል በማስቆጠር አዲስ ታሪክ አፅፏል ።

መቀሌ 70 እንደርታን በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ የማጣሪያ ጨዋታ ያለፈው የኢኳቶሪያል ጊኒው ካኖ ስፖርት በማጣሪያው ከግብፁ አል አህሊ ጋር ተገናኝቷል ።

በተመሳሳይ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ እየተሳተፈ የነበረው ፋሲል ከነማ ትናንት ከሜዳው ውጭ ታንዛኒያ ላይ በባለሜዳው አዛም ተሸንፎ ከውድድሩ መውጣቱ የሚታወስ ሲሆን ሁለቱም ክለቦቻችን ያስመዘገቡት ውጤት የሀገራችን እግርኳስ ድምር ውጤት በመሆኑ ሳንሰራ የተሻለ ውጤት መጠበቅ የዋህነት ነው።

www.AmharaSport.net

error: እባክዎትን ኮፒ ሲያደርጉ ምንጭ ይጥቀሱ!