የኢትዮጵያ  ከፍተኛ ሊግ ውድድር የሚጀምርበት ቀን ታውቋል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አሊሚራህ መሐመድ በ2012 የሚጀመረውን የከፍተኛ ሊግ ውድድር በተመለከተ ዛሬ ጥቅምት 27 ቀን 2012 ዓ.ም ወሎ ሰፈር በሚገኘው የፌዴሬሽኑ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ ጋር በተለያዩ ጉዳዩች ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በእለቱ የፌዴሬሽኑ ኘሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ፣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የማርኬቲንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አበበ ገላጋይ እንዲሁም አዲስ እና ነባር የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል፡፡

በስብሰባው ላይ የተገኙት ኘሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ለአባላቱ ይህ ስራ የሁላችን እንደመሆኑ አቅም በፈቀደ መልኩ የተሻለ እንዲሆን የበኩላችንን ማድረግ ይገባል፡፡ የመወዳደሪያ ሜዳን በተመለከተ ልዩ ትኩረት በመስጠት የበኩላችሁን ክትትል በማድረግ ሥራ እንዲሰራ እና አስተዳደራዊ ጉዳዩችን በተመለከተ በጋራ እየመከርን እንደምንሰራ እየገለጽኩ መልካም የሥራ እና የውድድር ጊዜ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ይህ ውድድር የተጀመረበት ጊዜ ቅርብ ቢሆንም በተለያዩ ማህበረሰብ ከፍተኛ ትኩረት እና ተደራሽነቱ ሰፊ የሆነ ውድድር ከመሆኑም በላይ ለኘሪሚየር ሊጉ በርካታ ክለቦችን ከማፍራቱ በተጨማሪ ለእግር ኳስ ስፖርቱ ትልቅ ሚናን እየተጫወተ የሚገኝ ነው፡፡ በዚህም የውድድር ደንቡን ከዲስኘሊን መመሪያው ጋር የሚናበብ በማድረግ ለክለቦች በሚደርሰው ኮሚኒኬ የክለቦችን ተደራሽ የማድረግ ሥራ በመስራት ውድድሩን የተበጠ ማሳደግ እንደሚቻል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የማርኬቲንግ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አበበ ገላጋይ አስረድተዋል፡፡

የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አሊሚራህ መሐመድ ለኮሚቴው አባላቱ አዲስ ከተቋቋመው የሊጉ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን በ2012 ዓ.ም ፌዴሬሽኑ ከሚመራቸው ውድድሮች መካከል ከፍተኛ የሆነውን የከፍተኛ ሊግ ውድድር ለመምራት ጠንካራ ሥራ እንሰራለን፡፡ ትልቅ ትኩረት ግን ልንሰጠው የሚገባው ነገር የመወዳደሪያ ሜዳ እንደመሆኑ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦችን ቢያንስ ለውድድሩ እጅግ ወሳኝ እንደ መወዳደሪያ ሜዳ አጥር ፣ የመፀዳጃ እና የመልበሻ ክፍል ያሉትን መገምገም ይገባል ሲሉ ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም በስብሰባው ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ የሚከተሉ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡

1. የ2012 ዓ.ም የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ምዝገባ እስከ ህዳር 8 ቀን 2012 ይጠናቀቃል እንዲሁ
2. የከፍተኛ ሊግ የዳኞችና ኮሚሽነሮች የክለቦች ክፍያ እስከ ህዳር 15 ቀን 2012 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡
3. የ2012 ዓ.ም የከፍተኛ ሊግ ውድድር የዕጣ ማውጣት ስነ-ሥርዓት ህዳር 20 ቀን 2012 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡
4. የቅድመ ሥራዎች ተጠናቀው ውድድሩ ህዳር 27 ቀን 2012 ዓ.ም የሚጀመርበት ይሆናል፡፡

©አማራ ስፖርት

error: እባክዎትን ኮፒ ሲያደርጉ ምንጭ ይጥቀሱ!