ከስጋቶች ይልቅ ተስፋዎችን የያዘው የ2012 ኘሪምየር ሊግ ነገ ይጀመራል

የ2012 ዓ/ም የኢትዮጵያ ወንዶች ኘሪምየር ሊግ በስጋቶች ተከቦም ቢሆን በርካታ ተስፋዎችን ይዞ ነገ በሚካሄዱ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ሊጉ ይከፈታል ።

ከባለፈው ዓመት የኘሪምየር ሊጉ ማብቂያ ጀምሮ የኘሪምየር ሊጉ እጣ ፋንታ በተለይም የአዲስአበባ ክለቦች ከፀጥታ ጋር በተያያዘ ተዟዙረን ለመጫዎት ስጋት አድሮብናል በሚል የክልል ሻምፒዮና ውድድር ይጀመር ሲሉ የክልል ክለቦች በበኩላቸው የሊጉ ፎርማት መቀየር የለበትም በሚል ለአራት ወራት ያህል በርካቶችን ሚዲያውንም ጨምሮ በሁለት ጎራ ሲያከራከር ቆይቶ በመጨረሻም በስፖርት ኮሚሽን ውሳኔ ሊጉ እንዲቀጥል መደረጉ ይታወቃል ።

ለኘሪምየር ሊጉ ትልቅ ስጋት ከሆኑት መካከል የአንዳንድ የክልል ስታዲየሞች የፀጥታ ጉዳይ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል ። ይሄ ስጋት ደግሞ የተጓዥ ደጋፊዎችን ክለብ የበለጠ የሚያሳስብ ሲሆን በቀጣይስ የሊጉ ስጋት ወይስ ተስፋ ይሆናል የሚለውን ነገ ማየት እንጀምራለን ።

የአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ላይ የታየው የደጋፊዎች ስፖርታዊ ጨዋነት በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በመቀሌና ፋሲል ደጋፊዎችም መታየቱ ምናልባትም እግርኳሳችን በፖለቲካ የምትናጠውን ሀገር ሰላም ይመልስ ይሆን የሚል ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል ።

ሌላኛው ተስፋ አብዛኞቹ ክለቦች በክረምቱ ተጠናክረው ለዚህ ውድድር እንደመቅረባቸው ሜዳ ላይ ከምንጊዜውም በላይ ተመልካችን የሚስብ ጨዋታዎችን ልንመለከት እንደምንችል ይገመታል ።

ኘሪምየር ሊጉ ነገ በሚካሄዱ 6 ጨዋታዎች የሚጀመር ሲሆን የሊጉ እንግዳ አዲስ አዳጊው ወልቂጤ ከተማ በሜዳው ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ይጫዎታል ።የአምናው ሻምፒዮን መቀሌ 70 እንደርታ በሜዳው አዲስ አዳጊውን ሀዲያ ሆሳዕና ሲያስተናግድ ሲዳማ ቡና ወደ ሶዶ አቅንቶ ባለሜዳውን ወላይታ ድቻ ይገጥማል ።

ሌላኛው የሊጉ ሶስተኛው እንግዳ ክለብ የሆነው ሰበታ ከተማ ወልዋሎን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ባለሜዳ ሰበታ ቢሆንም በሜዳ እድሳት ምክንያት ይሄ ጨዋታ አዲስአበባ ላይ እንደሚደረግ ታውቋል ።በሳምንቱ አጋማሽ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ያነሳው ፋሲል ከነማ ወደ ስምጥ ሸለቆዋ አዳማ ከተማ አምርቶ ከባለሜዳው አዳማ ከተማ ጋር ይጫዎታል።

ሁሉም ጨዋታዎች በተመሳሳይ 9:00 ላይ የሚደረጉ ሲሆን ጅማ አባጅፋር ከ ባህርዳር ከተማ ሰኞ የሚያደርጉት ጨዋታ ጅማ በቅጣት ይሄን ጨዋታ በአዳማአበበ ቢቂላ ስታዲየም ያካሂዳል ። ስሁል ሽረ በሜዳው ኢትዮጵያ ቡናን የሚያስተናግድበት ጨዋታ በትግራይ አለምአቅፍ ስታዲየም ይካሄዳል ።

www.AmharaSport.net

error: እባክዎትን ኮፒ ሲያደርጉ ምንጭ ይጥቀሱ!