ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

ባለፈው ሳምንት የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን በማንሳት ጥምር ድል ያስመዘገበው ፋሲል ከነማ ከባለሜዳው አዳማ ከተማ ጋር ነገ የሚገናኝበትና ከኘሪምየር ሊጉ የመክፈቻ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክር ይስተናገድበታል ።

ባለፈው ዓመት ፋሲል ከነማ የኘሪምየር ሊጉን ዋንጫ ካጣበት ምክንያት አንዱ 28ኛው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋራበት ሲሆን በዚህ ሜዳ ያጣውን ድል ለመመለስ ይሄን ጨዋታ በጥሩ አጋጣሚ ተጠቅሞ የውድድር ዓመቱን መጀመሪያ ከሜዳው ውጭ ጨዋታ ውጤት ይዞ ለመመለስ አልሞ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታሰባል ።

ሁለቱም ቡድኖች የባለፈው ዓመት አሰልጣኞቻቸውን ቀይረው በአዲስ አሰልጣኝ እየተመሩ ውድድሩን የሚጀምሩ ቢሆንም በቅርቡ በአዳማ ዋንጫ በተገናኙበት የደረጃ ጨዋታ ያለ ግብ ጨዋታው ተጠናቆ በመለያ ምት አዳማዎች አሸንፈው ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀው ነበር ።

በነገው ጨዋታ በአሸናፊ በቀለ የሚመራው ባለሜዳው አዳማ ከተማ በጥሩ መነቃቃትና የማሸነፍ ስነ ልቦና ላይ ከሚገኘው ፋሲል ጋር እንደመጫዎቱ ጥብቅ መከላከልን እንደሚተገብርና በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማግኘት እንደሚጫዎት ይገመታል ። እንግዳዎቹ ፋሲሎችም ቢሆኑ ግብ ላለማስተናገድ ለኋላ ክፍላቸውን ደህንነት ለማስጠበቅ ቅድሚያ መስጠታቸው የማይቀር ቢሆንም ቡድኑ የባለፈው ዓመት ጥንካሬውን ለማሳየት የግድ ከዚህ ጨዋታ ውጤት ይዞ መመለስ ይጠበቅበታል ።

የዚህን ጨዋታ የበላይነት ከመውሰድ በተጨማሪ ውጤት ይዞ ለመውጣት መሀል ሜዳ ላይ ያለውን ብልጫ ለመውሰድ በሚደረገው ፉክክር የቀድሞ ጓደኛሞቹ የፋሲሉ ሱራፌል ዳኛቸው እና የአዳማው ወጣቱ አማካይ ከንዓን ማርክነህ የመሃል ሜዳ ፉክክር ይጠበቃል ።

በፋሲል ከነማ በኩል አብዱራህማን ሙባረክና እንየው ካሳሁን በጉዳት ለዚህ ጨዋታ ግልጋሎት እንደማይሰጡ ሲረጋገጥ ሌሎች ተጨዋቾች በሙሉ ጤንነት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው ።

የባለሜዳዎቹን የጉዳት ዜና ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም ።

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 6 ጊዜ ተገናኝተው ተመጣጣኝ ውጤት አላቸው ። አራት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈዋል ። በግንኙነታቸው በጋራ ስድስት ጎሎች ተቆጥረዋል ።

– አዳማ ላይ በተገናኙበት 3 ጨዋታዎች በአንዱ አዳማ ከተማ ሲያሸንፍ በሁለቱ በአቻ ውጤት ነጥብ ተጋርተዋል ። ጎንደር ላይ 3 ጊዜ ተገናኝተው በአንዱ ፋሲል ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል ።

– ሁለቱ ቡድኖች ቅርብ ጊዜ የተገናኙት በአዳማ ዋንጫ ሲሆን ያለ ጎል 0 – 0 በሆነ የአቻ ውጤት ተለያይተዋል ።

www.AmharaSport.net

error: እባክዎትን ኮፒ ሲያደርጉ ምንጭ ይጥቀሱ!