“ካፍ እቅዳችንን እንድንከልስ አድርጎናል” ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ

የኢትዮጵያ ወንዶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በዛሬው እለት ማለትም ጥር 15/2012ዓ.ም ወሎ ሰፈር በሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት በመገኘት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠዋል። ጋዜጣዊ መግለጫው በሁለት አበይት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።

እነዚህም የካፍ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላይ ያደረገው የፕሮግራም ማሻሻያ እና የዓለም ዋንጫ የምድብ ድልድልን የተመለከቱ ናቸው።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ የአፍሪካ ዋንጫ የሚደረግበት ጊዜ በወርሃ ጥር በቀደመው መልኩ እንዲካሄድ መወሰኑን ተከትሎ የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች የሚደረጉበት ቀናት ላይ ማሻሻያ ማደረጉ ይታወቃል። ይህንንም አስመልክቶ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የማከተሉትን ሀሳቦች በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት አንስተዋል።

“ካፍ ያደረገው የፕሮግራም ማሻሻያ የአፍሪካ ዋንጫው ማጣሪያ ወደ መጋቢት ወር እንዲመጣ አደርጎታል በመሆኑም ካለን ጊዜ አንጻር እቅዳችንን እንድንከልስ አድርጎናል። የወዳጅነት ጨዋታዎችን በተለይ ከኒጀር ጨዋታ በፊት ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን በሜዳችን እና ከሜዳችን ውጭ ለማድረግ አስበናል ይህንንም ለማሳካት የተለያዩ ጥረቶችን በማከናወን ላይ እንገኛለን። ከኮትዲቯር ጨዋታ በኋላ የወዳጅነት ጨዋታ ጥያቄ ያቀረቡልን የሰሜን እና የምዕራብ አፍሪካ ቡድኖች አሉ። ፕሪሚየር ሊጉን ከሚመራው አካል ጋር በመነጋጋር በሳምንት ሁለት ቀናት የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች የልምምድ ፕሮግራም ማክሰኞ እና ረቡዕ እንዲኖራቸው ለማድረግ አስበናል። ይህም የተጫዋቾችን ወቅታዊ ብቃት በቅርበት ለመከታተል ያስችለናል ብሎም በየጊዜው የሚቀያየረው የተጫዋቾች ምርጫ ወጥነት ያለው ብሄራዊ ቡድን እንዲኖረን ያደርጋል። ይህ በሳምንት ሁለት ቀናት የሚደረገው ልምምድ በንድፈ ሀሳብ እና በሜዳ ተግባራት የታገዘ እንዲሆን አቅደናል። ስፖርት ኒውትሪሽን እና ስፖርት ሳይኮሎጂ ጋር የተያያዙ እንዲሁም ከብሄራዊ ቡድኑ አጨዋወት ጋር ከታክቲክ ጋር የተያያዙ ትምህርቶችንም ለብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች የምንሰጥ ይሆናል።”
የኳታር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ድልድል በቅርቡ ይፋ በሆነበት ወቅት ኢትዮጵያ ከጋና ደቡብ አፍሪካ እና ዙምባብዌ ጋር በምድብ 7 መደልደሏ ይታወቃል። የምድብ ድልድሉን አስመልክቶ ኣንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የሚከተለውን ሀሳብ ሰጠዋል። “ያለንበት ምድብ ጠንክረን እንደንሰራ እና ምድቡን የሚመጥን ዝግጅት እንድናደርግ የሚጠቁም ነው። ውድድሩን በጥሩ ተሳትፎ ከምድባችን ለማለፍ የሚያስችሉ ነጥቦችን ነድፈን እንቀሳቀሳለን። ግብአት ለማሰባሰብ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ግብዓቶችን እናሰባስባለን። ከሚዲያ አካላትም ጋር ውይይት በማድረግ ግብዓት እናሰባስባለን። ለአለም ዋንጫ ለማለፍ የሚለው ስያሜ በራሱ እኛም ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ እኛም ስራችንን እንሰራለን።”
ከጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ምላሽ ሰጠውባቸዋል።

Via EFF

www.amharasport.net

error: እባክዎትን ኮፒ ሲያደርጉ ምንጭ ይጥቀሱ!